በተ አማራ መድህን ከጥቂር ወራት በፊት ሶስት በአማራ ስም የተደራጁ ድርጅቶች በጋራ ተዋህደው የመሰረቱት ድርጅት ነው። ድርጅቱ በአገር ቤት የሕቡእ መዋቅር ያለው ሲሆን በዉጭ አገርም በአሜሪካ፣ በአዉሮፓ፣ በአፍሪካና በአውስትራሊያ በአገር ቤት ያለውን ትግል ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ያለ ድርጅት ነው። ቤተ አማራ መድህን በአማራ ስም የተደራጀና በአሁኑ ወቅት በተለየ መልኩ በአማራው ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ለመከላከል የሚስራ ቢሆንም፣ የመጨረሻ ግቡ ለሁሉም አማራዉን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እኩል የሆኑባት፣ ዜጎች በማንኛውም የአገሪቷ ክፍል በነጻነት የመኖር መባታቸው እንዲጠበቅና አሁን ያለው የዝር ፖለቲካ በዘር ላይ የተመሰረተ ፌዴራል አወቃቀር እንዲቀየር ለማድረግ እንደሆነ የአመራር አባላቱ በይፋ እየገለጹ ነው።
ቤተ አማራ መድሕን በወያኔ ሰራዊት ወቅታዊ ፖለቲካዊ ስብዕናና ሞራሉ ላይ ያደረገው ግምገማና ጥናት ውጤት
የቤተ አማራ መድህን መረጃና ዘመቻ መምሪያ በወያኔ የእግረኛ ሰራዊት ወቅታዊ አደረጃጀት፣ ስምሪትና የውጊያ ብቃት ላይ ጥናታዊ ግምገማወችን አድርጓል፡፡ ዝርዝር የጥናት ውጤቱን የድርጅታችን የመረጃና ዘመቻ መምሪያ ለድርጅታዊ ተልኮ የሚጠቀምበት ሁኖ የሰራዊቱን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ስብእናና ሞራሉ ላይ ያገኘውን ተጨባጭ መረጃ በአጭሩ በአጭሩ ከፋፈለን አዘጋጅተን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡
የቤተ አማራ መድህን መረጃና ዘመቻ መምሪያ ባካሄዳቸው ጥናቶችና ግምገማወች የእግረኛ ሰራዊቱን ሁኔታ በሚመለከት ያጠናናቸውን ጥናቶች በሚመለከት ወያኔን ለማስወገድ ለሚታገሉ ሃይሎች ሁሉ ለመነሻነት ይጠቅማል ብለን ስለምናስብ መረጃውን ሙሉ በሙሉ ለማግኘትና ለመጠቀም የምትፈልጉ የነጻነት ሀይሎች ድርጅታችንን በቀጥታ መገናኘት እንደምትችሉ እየገለጽን መረጃውን ስናጋራ ትክክለኛ መሆኑንም በማረጋገጥ ነው።
ክፍል አንድ፡- የሰራዊቱ ፖለቲካዊ ስብዕናና ሞራል
ሰራዊቱ በወያኔ መንግስት ላይ ያለዉ እምነት ዝቅተኛና በአመዛኙ በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ነዉ፡፡ ወታደሩ በዉትደርና ህይወቱ እጅግ የተሰላቸ ነዉ፡፡ የተለያዩ ሰበቦችን እየተጠቀመ ሰራዊቱን መልቀቅ ይፈልጋል። ክዳት እጅግ ሰፊና ተደጋጋሚ ነው። የእርስበርስ መገዳደል ቀላል አይደለም። ከትግሬ ዉጭ ያለዉ የሰራዊት ክፍል (ዝቅተኛው አመራርና ወታደር) የመንግስት ለዉጥ እጅግ ይፈልጋል፡፡ የሰራዊቱ ዉስጣዊ አንድነት፣ መተማመን፣ ሞራል ሁሌም በችግር የተሞላ ነዉ፡፡ አንድም ጊዜ መሻሻል አለ ተብሎ የተገመገመበትን ጊዜ ማስታወስ አይቻልም፡፡ ሰራዊቱ የህወሃት የበላይነት በሚፈጥረዉ አድሎኛና ዘረኛ አካሄድ እጅግ የተማረረ ነዉ፡፡ ከሸማቂዎች ጋርም በጀግንነት እስከ መጨረሻ ይዋጋል ተብሎ አይገመትም፡፡ ባደረግነው ጥናት ሰራዊቱ ከኤርትራ ሰራዊት ጋር ሊዋጋ እንደሚችል የጥናት ግምገማወች ያሳያሉ፡፡
ይህ ግን ከኢትዮጵያዊያን ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣዉ ብሄራዊ ጀግንነት የሚመነጭ እና በአጋጣሚው ስርዓቱን መቀየር ያስችላል ከሚል እንጅ ስርአቱን ለመከላከል ከመቁረጥ የሚነሳ ግን አይደለም፡፡ የሰራዊቱ ቁጥር አንድ ፖለቲካዊ ችግር መገለጫ ተደርጎ ሁሌም የሚገምገመዉ ክዳት ነዉ፡፡ በ2006 ላይ ክዳት የሚለዉ አይገልጸዉም ተብሎ መፍረስ በሚለው ደረጃ ነበር የተገመገመዉ፡፡ አመታዊ ፈቃድ ሄዶ የማይመለሰዉ እጅግ ብዙ ነዉ፡፡ በቀጥታ ከሰራዊቱ ተነስቶ ከነመሳሪያው የሚከዳዉም ከፍተኛ ነዉ፡፡
በየደረጃዉ ያለዉ አመራር ሁሌም እንደተሳቀቀ የሚኖርበት ችግር የሰራዊት ክዳት ነዉ፡፡ ግምገማ በተጠራ ቁጥር የከጂ ብዛት ሪፖርት ይዞ መቅረብ የግድና የተለመደ ነዉ፡፡ ከጂ የለኝም የሚባል ሪፖርት በሁሉም ክፍሎች አይታወቅም፡፡ ለምሳሌ ተጨባጭ መረጃ ለመጥቀስ ያህል ከ1995 መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ግንቦት 2001 ዓ.ም ድረስ በጥቅሉ 74797 ወታደሮች ከድተዋል፡፡ ከዚህ የከጂዎች ቁጥር ዉስጥ 597 የሚሆኑት ከብ/ጀነራል እስከ ምክትል መቶ አለቃ ያሉ መኮንኖች ናቸዉ፡፡ በተለያየ ወንጀል የታሰሩ 1939 ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ታሳሪዎች መካከል 64 የሚሆኑት ከኮሎኔል እስከ ምክትል መቶ አለቃ ያሉ ወታደራዊ መኮንኖች ናቸዉ፡፡ ይህ እንግዲህ በማእከል ደረጃ የታሰሩትን ብቻ የሚመለከት ቁጥር ነዉ፡፡ በዚያዉ ዘመን 14492 የሰራዊት አባላት ከሰራዊቱ ተባረዋል፡፡ ከዚህ የተባራሪዎች ቁጥር ዉስጥ 459 የሚሆኑት ከኮሎኔል ጀምሮ በተዋረድ የሚገኙ መኮንኖች ናቸዉ፡፡ በሶስቱም ምክንያቶች ማለትም በክዳት፣ በመባረርና በእስር ከሰዉ ሃይል እንዲወገዱ የተደረጉት የባለሌላ ማእረግተኞች ብዛት 27221 ሲሆን የተቀረዉ 62141 የሰዉ ሃይል ደግሞ ተራ ወታደር ነዉ፡፡
ከላይ የተጠቀሰዉ መረጃ ከመከላከያ የሰዉ ሃብት ልማት ዋና መምሪያ የተወሰደ ተጭባጭ መረጃ ነዉ፡፡ ይህ ቁጥር የችግሩን አሳሳቢነት ሲገመገምና ጥናት ሲደረግ የተሰጠ ተጨባጭ መረጃ በመሆኑ ነዉ፡፡ ነገር ግን መታወቅ ያለበት ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ነዉ፡ ምክንያቱም በመከላከያ ዉስጥ ያለዉን ዝርክርክ የሰዉ ሃብት ክትትል ስርአትና አሰራር የምናዉቅ ሁሉ ይህ ቁጥር ከእዉነታዉ ያነሰ እንደሚሆን ይገመታል፡፡
ለምሳሌ በአማራ ስም ተደራጅተዉ መፈንቅለ መንግስት ሊያካሂዱና ሲያሴሩ ታሰሩ የተባሉት ሁለት ብ/ጀነራሎችና፣ ከአርባ በላይ የሚሆኑት ከፍተኛ መኮንኖችና በርካታ ወታደሮች የታሰሩት ሚያዝያ 2001 ዓ.ም ቢሆንም በግምገማ ሪፖርቱ ዉስጥ ግን አልተካተቱም ነበር፡፡ የ1997 ዓ.ም ሃገር አቀፍ ምርጫን ተከትሎ በነበረዉ የፖለቲካ ቀዉስ በቅንጀትነትና በኦነግነት ተፈርጀዉ ሁለት ሜ/ጀነራሎችና ሁለት ብ/ጀነራሎች 1999 ዓ.ም መባረራቸዉ የሚታወቅ ቢሆንም በተመሳሳይ መንገድ ሪፖርቱ ዉስጥ አልተገለጹም፡፡ እንዲህ አይነት የተዝረከረከ የሰዉ ሃይል መረጃ አያያዝ በጀነራልና በከፍተኛ መኮንኖች ደረጃ ከታየ በመስመራዊ መኮንኖች፣ በበታች ሹሞችና በወታደሮች ደረጃ ምን ያህል ሰፊ መዝረክረክ ሊኖርበት እንደሚችል ማንም መገመት ይችላል፡፡ ጥር 2003 ዓ.ም በተደረገ የሰራዊት ፖለቲካዊ ሁኔታ ግምገማ ደግሞ በቀደሙት አራት አመታት ብቻ ከ101 ሺህ የሰራዊት አባላት በላይ መክዳታቸዉን የሚያስረዳ መረጃ የዚህ ሪፖርት አዘጋጆች በተገኙበት ግምገማ ቀርቦ ነበር፡፡
በእነዚህ አመታት መከላከያ የቀጠራቸዉ አዳስ ወታደሮች በጥቅሉ 100 ሺህ የነበረ ሲሆን የከጂዉ ብዛት ግን በአንድ ሺህ ይበልጣል ተብሎ ነበር የተገመገመው፡፡ ይህ አንግዲህ በቀጥታ የከዳዉን ብቻ የሚመለከት ቁጥር ነዉ፡፡ የሚባረረዉ፣ የሚታሰረዉ፣ በቦርድና በጡረታ የሚገለለዉ፣ በዉጊያና በልዩ ልዩ አደጋ ምክንያት ህይወቱ አልፎና ጉዳት ደርሶበት ከተዋጊ ሃይል የሚቀነሰዉ ሃይል ሲጨመርበት የሰዉ ሃይሉን ኪሳራ የት ሊያደርሰዉ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ አንድ የመቶ 8 ቢበዛ 12 ወታደሮችን ብቻ ይዞ ነበር የመቶ እየተባለ ይጠራ የነበረዉ፡፡ ከጥር 2005 እስከ መስከረም 2006 ባሉት ወራት ሁሉም ክ/ጦር ኮማንድ በተገኘበት በመከላከያ ደረጃ ለሶስት ጊዜ ግምገማዎች የተደረጉትም ክዳትን ማስቆም አይደለም በየአመቱ እየተባባሰ የሚሄደዉ ለምንድነዉ በሚል ነበር፡፡
በመሆኑም ሁኔታዉ በዚህ መንገድ ከቀጠለ የሚያስከትለዉ ዉጤት አደገኛ በመሆኑ ክዳትን ማስቆም ያልቻለ አመራር ቦታዉን ይልቀቅ የሚል የቁጣ ግምገማ ከመከላከያ ጀምሮ እስከ ዝቅተኛ የጦር ክፍሎች ድረስ እንዲካሄድ ነበር በጀ/ል ሳሞራ ትዕዛዝ የተሰጠው፡፡
እያንዱንዱ የጦር አመራር ያለዉን የከጂ ቁጥር ቆሞ በስብሰባዎች ሪፖርት እንዲያደርግ ነበር የተደረገዉ፡፡ ተዋጊ ሰራዊት የሌለዉ የሰራዊት አመራር ፋይዳ የለዉም፤ በስራዉ መቀጠል የፈለገ ክዳትን ያስቁም፤ ካልቻለ ደግሞ ቦታዉን ለሚችል አመራር ይልቀቅ፤ ከዚህ በሗላ ያስከዳ የማእረግም ሆነ የሃላፊነት ሹመት አይሰጠዉም ወዘተ በሚል ነበር የተገመገመዉ፡፡ ግምገማዉ እንደተጠናቀቀም ክዳት የሌላቸዉን የጦር ክፍሎች የመለየት ስራ እንዲሰራ ተደረገ፡፡ የመለየት ስራዉ የተካሄደዉ ለመሸለም ታስቦ ነበር፡፡ ፍለጋ ሲጀመር በአንድ አመት ጊዜ ዉስጥ ክዳት ያልተመዘገበባቸዉን ሬጅሜቶች ሳይሆን ሻምበሎችን ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ አለመኖሩ ተረጋገጠ፡፡ ዕዝን ከሚያክል ግዙፍ የጦር ክፍል ዉስጥ ያላስከዳ የጦር ከፍል ማግኘት የተቻለዉ በመቶና በጓድ ደረጃ ከሚገኙ በጣት ከሚቆጠሩ የጦር ክፍሎች ብቻ ነበር፡፡ አመራሩ ያላስከዱ ሻምበሎችን ለማግኘት ሲል ቀደም ሲል ከድተዋል በሚል ሪፖርት የተደረጉ አባላትን ሳይቀር ለመደበቅ ብዙ ጥረት ማድረግ የጀመረበት ሁኔታ ነበር፡፡ አልከዳም ብሎ ለማስተባበል የቸገረዉ ደግሞ ከክዳት በራሱ መንገድ ተመልሷል ወይም ታድኖ ተይዞ እንዲመለስ ተደርጓ በሚል ለመሸፋፈን ነበር ጥረት የተደረገዉ፡፡
በዚህ መንገድ በተካሄደ የማጣራት ስራ አላስከዱም በሚል የተለዩ የመቶዎችንና ቲሞችን ለመሸለም ጀነራል ሳሞራ ወደ ዕዞች ተራ በተራ እየተጓዘ ቴሌቪዥን፣ ዲቪዲ፣ የዜና ራዲዮና ክዳትን ያስቆመ ጀግና የሚል የምስክር ወረቀት እንዲሸልም ነበር የተደረገዉ፡፡ በጥቅሉ አመታትን በዘለቀ ተደጋጋሚና አሰልች ዉይይትና ግምገማ ክዳትን ለማስቆም ብዙ ጥረት ቢደረግም የሚቻል አልሆነም ብቻ ሳይሆን ከአመት አመት እየተባባሰ በመሄድ ላይ ነው ያለው፡፡ ይህም ከስርአቱ ጋር ምን ያህል የተጣላ መሆኑን የሚያሳይ ነው። በክዳት መልክ ሰራዊቱን ከሚለቀዉ በተጨማሪ በልዩ ልዩ መንገድ ከሰራዊቱ ለመዉጣት የሚደረገዉ ጥረትም እጅግ ሰፊ ነዉ፡፡ በቦርድ ለመልቀቅ ህክምና የሚመላለሰዉ፣ በሰባት አመትና በአስር አመት አገልግሎት ለመልቀቅ የሚሰለፈዉ፣ ስታፍ ለመመደብ የሚታገለዉ፣ በሰላም ማስከበር ሽፋን ወደ ውጭ ለመውጣት የሚጥረው፣ በትምህርት ስም ገለል ለማለት የሚፈጋዉ፣ የመኮንነት ስልጠና ላለመግባት የመግቢያ ፈተናዉን ሆን ብሎ የሚወድቀዉ ወዘተ ብዙ ነዉ፡፡ ከ2001 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገዉ የሰባትና የአስር አመት አገልግሎት ያጠናቀቁ የሰራዊት አባላትን ከሰራዊት የማሰናበት ዉሳኔን ተከትሎ አገልግሎቱን የጨረሰዉ ሰራዊት ብቻ ሳይሆን ያልጨረሰዉ ጭምር ሰራዊቱን ለመልቀቅ ሰልፍ የያዘበት ሁኔታም መከላከያ ይሆናል ብሎ ከገመተዉ ፍጹም የተለየ ነበር፡፡
አሁንም ድረስ በየአመቱ ለመዉጣት ያለዉ ሰልፍ ጦርነት ነዉ፡፡ በየአመቱ የሚታየዉ የልቀቁኝ ልመና፣ አብዮትታና ጭቅጭቅ ለማመን የሚከብድ ነዉ፡፡ ሰራዊቱ ከመከላከያ የተሻለ የስራ እድል የሚያገኝበት ሁኔታ ስለሌለ የትም አይሄድም የሚል ከፍተኛ ግምት የነበረ ቢሆንም በተግባር የታየዉ ግን ባንዴራ ተዘርግቶ ጥላችሁን ለመሄድ የወሰናችሁ ባንደራዉን ተራምዳችሁ ሂዱ ወደ ሚል ልመናና ለቅሶ ነበር የተገባው፡፡ ይህም አልሆን ሲል እነማን ቀድመዉ እንደሚሄዱ አመራር ይወስን ተብሎ በመመሪያ ነበር ተግባራዊ የተደረገዉና አሁንም ድረስ የሚደረገዉ፤
እነዚህ ሁሉ ችግሮች ሰራዊቱ ዉስጥ ያለዉን የሞራል መዉደቅና የእምነት መሸርሸር መኖሩን የሚያረጋግጡ ምልክቶች ናቸዉ፡፡ አብዛኛዉ የበታች አመራርና ወታደር በዉትድርና ህይወቱ ደስተኛ አይደለም ክፍል ሁለት ሰሞኑን ይቀጥላል፡፡